ባህር ዳር – ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከስደት ተመላሽ የሆኑ፣ በሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር የተጎዱ እንዲሁም ልዩ ልዩ ጥቃቶች የደረሰባቸው ከ240 ሺህ በላይ ዜጎችን ከቀውስ የታደገው አንጋፋው ሀገር በቀል ድርጅት አጋር ኢትዮጵያ፤ በአማራ ክልል የሚሰጠውን ሁለንተናዊ የሰብአዊ ድጋፍ አገልግሎት ይበልጥ ለማስፋፋት የሚያስችለውን ታሪካዊ የስምምነትና የህንፃ ርክክብ በባህር ዳር ከተማ በይፋ ፈጽሟል።
ተቋሙ በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ ወገኖች አስተማማኝ መጠለያ በመስጠት፣ የሕክምና፣ ጥልቅ የስነ-ልቦና ምክር እና የሙያ ስልጠና ድጋፎችን በመለገስ ወደ መደበኛና አምራች ሕይወታቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ ሰፊ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
አጋር ኢትዮጵያ በባህር ዳር ከተማ ላለፉት 8 ዓመታት አገልግሎቱን በኪራይ ቤት ውስጥ ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ግን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ያስገነባውን ዘመናዊና ባለብዙ አገልግሎት ሕንፃ “የልህቀት ማዕከል” (ሴፍ ሀውስ) በይፋ ተረክቧል። ይህ ርክክብ ማዕከሉ ያለበትን የቦታ ጥበት በመቅረፍ የድጋፍ አድማሱን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ያስችለዋል።

የአጋር ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር አምባሳደር ዶ/ር አበራ አደባ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ተቋሙ ከመላው ኢትዮጵያ ለሚመጡ ተጎጂ ዜጎች በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በሚገኙ ስትራቴጂካዊ ማዕከላቱ አማካኝነት አገራዊ ሰብአዊ ግዳጁን በስፋት እየተወጣ ይገኛል። አክለውም፣ ካለው የችግሩ አሳሳቢነትና ስፋት አኳያ እነዚህን ማዕከላት ማስፋፋት እና ማባዛት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ደረጃ በደረጃ ከዕርዳታ ጥገኝነት ወደጸዱና ራሳቸውን ወደቻሉ የልህቀት “ማኅበራዊ ኢንተርፕራይዞች” (Social Enterprises) ለመለወጥ የሚያስችሉ ስልታዊ ዕቅዶች ተነድፈው ወደ ተግባር እየተገባ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ዶ/ር አበራ አደባ የክልሉ መንግሥት ለአጋር ኢትዮጵያ ለሰጠው ከፍተኛ እምነትና ለጣለበት ትልቅ አደራ ልባዊ ምስጋና አቅርበው፤ ተቋሙ ሁልጊዜም በሚመራበት “በትልቅ ማለም፣ በትንሹ መጀመር፣ አሁኑኑ መተግበር!” (“Think Big, Start Small, and Act Now!”) በሚለው መርሁ መሠረት የተጣለበትን አገራዊ አደራ በከፍተኛ ኃላፊነትና በታማኝነት እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።